ቀጥታ፡

በክልሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ያለመ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው

አዳማ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ያለመ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

ጽሕፈት ቤቱ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጋር በመተባበር በየደረጃው ያሉ የሴቶች አደረጃጀቶች የሚሳተፉበት የቦንድ ግዥ ንቅናቄ በክልል ደረጃ በአዳማ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።


 

የጽሕፈት ቤቱ ዳይሬክተር ወይዘሮ ቆንጂት በቀለ እንደገለፁት በክልሉ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ህዝቡ በቦንድ ግዥና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥና በድጋፍ ከ9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ መለገሱን ገልጸዋል።

በዘንድሮ ዓመትም ግድቡን ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ርብርብ ለማፋጠን በክልሉ በቦንድ ግዥና በድጋፍ እስከ መጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ከ500 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ከ484 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቅሰው የዛሬው ንቅናቄም ከፓርቲው ሴቶች ክንፍ ጋር የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ምክትል ሃላፊ ብዙአየሁ ደገፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው የህዝቦች አንድነት ተምሳሌት የሆነውን ግድብ ለማጠናቀቅ የፓርቲው የሴቶች ክንፍ 100 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ንቅናቄ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ዕቅዱን ለማሳካትም በየደረጃው ያሉ የሴቶች አደረጃጀት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ሃላፊ ወይዘሮ ሳሚያ አብደላ እንዳሉት የፓርቲው የሴቶች ክንፍ ግድቡ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው።

ዛሬ የተጀመረው የቦንድ ግዥ ንቅናቄም በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው የሴቶች ክንፍ አደረጃጀት፣ የሴቶች ፌዴሬሽንና ማህበራት የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በንቃት የሚሳተፉበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም