ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ከደረጃ በታች የሆኑና ችግር የተገኘባቸው ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ከደረጃ በታች የሆኑና ችግር የተገኘባቸው ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል - ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፦ ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ከደረጃ በታች የሆኑና ችግር የተገኘባቸው ምርቶች እንዲወገዱ መደረጉን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
በአልን ምክንያት በማድረግ ለገበያ በሚቀርቡ የተለያዩ ምርቶች ላይ ጥራትና ደህንንት ለማረጋገጥ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጿል።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የፋሲካ በዓል የፊታችን እሁድ ይከበራል።
የእምነቱ ተከታዮችም በአሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ምግብ ነክ ከሆኑ ምርቶች በተጨማሪ ሌሎች ግብአቶችን ከተለያዩ የገበያ ማዕከላት በስፋት ይገበያያሉ።
በባለስልጣኑ የምግብ ኢንስፔክሽንና ህግ ማስፈፀም ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙላቱ ተስፋዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራትና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል።
ባለስልጣኑ በአሉ ከመድረሱ አስቀድሞ ባደረገው ጥናትና ፍተሻ እንዲሁም ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ከደረጃ በታች የሆኑና ችግር የተገኘባቸው ምርቶች እንዲወገዱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለህብረተሰቡ በስፋት የሚቀርቡ ምርቶች በጤና ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም ከበአል ጋር ተያይዘው በስፋት ገበያ ላይ በሚውሉ እንደ በቅቤ፣ ማር እና ዘይት ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት መደረጉን ነው ያስረዱት።
ከምግብ ደህንነት መጓደል ጋር በተያያዘ ባእድ ነገሮችን ከመቀላቀል በተጨማሪ በአያያዝ ችግር ብልሽት እንደሚያጋጥምም አንስተዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ ከ20ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የተበላሸ በርበሬ እንዲሁም ከባእድ ነገር ጋር የተቀላቀለ ከ9ሺህ ሊትር በላይ ዘይት በቁጥጥር ስር በማዋል በአጥፊዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን አስታውቀዋል።
በጅማ፣ አጋሮ እና መቱ አካባቢ ከባእድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ የተገኘ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ምርት ላይ እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል።
ባለስልጣኑ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ከደረጃ በታች የሆኑና ችግር የተገኘባቸው ምርቶች እንዲወገዱ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ሸማቾች የሚሸምቷቸውን ምግቦችናና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ጥራታቸው የተጠበቀ መሆኑን በተገቢው መንገድ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ህብረተሰቡ ምርቶቹን በተመለከተ አጠራጣሪ ነገሮች ካጋጠሙት በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ወይም ለጸጥታ አካላት አፋጣኝ መረጃ እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።