ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- የደቡብ አፍሪካ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብንርን ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሊል ከድር ከደቡብ አፍሪካ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ምቶ ኩሉ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካን የኢንቨስትመንት ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
አምባሳደር ደሊል ለፕሬዝዳንቱ ስለ ኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎች እንዲሁም ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር መስራት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የደቡብ አፍሪካ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ምቶ ኩሉ የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የሚያጎለብቱ ምቹ እድሎች እንዳሉ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል።
በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በብሪክስ ፕላስ የቢዝነስ ምክር ቤት ማዕቀፍ በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።
በኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤቶች መካከል ቋሚ የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይቶችን ማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ ለመፍጠርም ተስማምተዋል።
የተያዙት እቅዶች ከዳር እንዲደርሱ የጋራ የቢዝነስ ምክር ቤት እንደሚቋቋም እና ውይይቶች እንደሚደረጉ መገለጹን በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።