የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የ3D ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን ወደ ኢትዮጵያ ሊያስገባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን 3D ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ለማስገባት በዘርፉ እውቅናን ካተረፈው ከኦስትሪያው ግዙፍ የግንባታ ቴክኖሊጂ አቅራቢ ባውሚት ግሩፕ ከተባለ ኩባንያ ጋር ተስማምቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማልኦስትሪያ ዎፊንግ ከተማ ከግንባታ ቴክኖሎጂ አቅራቢው ኩባንያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር 3D የኮንስትራክሽን ፕሪንትን ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ ለማድረግ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር አድርገዋል፡፡

አቶ ረሻድ ከማል ኮርፖሬሽኑ ለጀመረው ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ማስፋትና ማላመድ ስትራቴጂ ትግበራ ተጨማሪ ተሞክሮ ለመቀመር በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተሰናዳው የኮንስትራክሽን ማሽን እና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይም ተሳትፈዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በፊት የአልሙኒየም ፎርምወርክ የግንባታ ቴክኖሎጂን ከኦቪድ ጋር በመሆን ከኮርያ በማስመጣት በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለ ሲሆን የፕሪካስት የግንባታ ቴክኖሎጂን ከዋንኮ ኢታሊ ኩባንያ ጋር በመሆን ተግባራዊ ለማድረግም እየሰራ መሆኑንም ኮርፖሬሽኑ አመላክቷል፡፡


 

የአሀኑን ስምምነት ተከትሎ 3D ኮንስትራክሽን ፕሪንት የግንባታ ቴክኖሎጂ፡- ኮርፖሬሽኑ ለአገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያስተዋወቀው ሦስተኛው ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ መሆን ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

3D የኮንስትራክሽን ፕሪንት በአውሮፓና የእስያ አገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለ ሲሆን በአፍሪካም በማላዊና ኬንያ ጥቅም ላይ ውሎ ውጤታማነቱ ተረጋግጧል፡፡

በሀገራችንም አሁን ላይ እያደገ የመጣውን ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ፍላጎት እና በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየውን የግንባታ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ከኦስትሪያው ባውሚት ግሩፕ ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ እንደታመነብትም ተጠቁሟል

3D የኮንስትራክሽን ፕሪንት ከተለመደው የግንባታ ዘዴ ጋር ሲነጻጸር የግንባታ ወጪን ከግማሽ በላይ የሚቀንስና ውስብስብ አርክቴክቸራል የቤት ዲዛይኞችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደሆነም ተገልጿል፡፡


 

ቴክኖሎጂው 98 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ የሚጠቀም ሲሆን ግዙፍ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችንና የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን በወራት እድሜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

የመኖሪያ ቤት ቪላዎችን ደግሞ ከአንድ ቀን ባናሰ ጊዜ መገንባት የሚያስችል እንደሆነም ኮርፖሬሽኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለቸው የአዲስ አበባ ከተማና ትልልቅ ከተሞች በፍጥነት በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤትን ማቅረብ የሚያስችል በመሆኑ 3D ኮንስትራክሽን ፕሪንት የግንባታ ቴክኖሎጂ በአገራችን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ አዲስ አብዮት ሊፈጥር እንደሚችል ይጠበቃልም ነው ያለው፡፡

ቴክኖሎጂውን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረትም ባውሚት ግሩፕ ለኮርፖሬሽኑ በቀጥታ ድጋፍ የሚያደርግና በትብብር እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፋጻሚ የሚመራው የኮርፖሬሽኑ ልዑክ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችና ሀብት አስተዳደር ረገድ በታዋቂው ዓለም ዓቀፍ ኩባንያ ሎህበር አሶሼትስ እየተከናወነ ያለውን ጥናት ያለበትን ደረጃ በሙኒክ ከተካሄደው ኢግዚቢሽን ጎን ለጎን ምልከታና ውይይት አድርገዋል ብሏል፡፡


 

በየሦስት ዓመት በጀርመን ሀገር የሚካሄደው ግዙፉ የኮንስትራክሽን ማሽን እና ቴክኖሎጂ አለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ዓለማችን የደረሰችበትን ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና የላቀ ጥራት ያላቸው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓቶች፣ ማሽኖችና ቴክኖሎጂዎች ይፋ የሚደረጉበት ተደናቂ ትዕይንት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በጀርመን ሙኒክ ከተማ የተዘጋጀው "Bauma 2025" አለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ 57 አገራት የተውጣጡ 6ሺህ በላይ ታሳታፈዎች እና 3ሺህ በላይ ኩባንያዎች የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ ለእይታና ለግብይት ማቅረባቸው ተመላክቷል።

በዚህ ኢግዚቢሽን ከሁለንተናዊ ሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ የሚገኘው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከመሠል አለም አቀፍ ተቋማት ጋር ውይይት ከማድረጉም ባሻገር፣ ለቀጣይ ሥራዎቹ ልምዶችን እንዲቀምር እድል እንደፈጠረለትም ታውቋል።

አቶ ረሻድ ከዓለም የሥራ፣ የሙያ ጤና እና ደህንነት ድርጅት ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ካርል ሄንዝ ጋር በመገናኘት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ የሠራተኞች የሥራ ደህንነት ዙሪያ ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውንም ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም