የኢትዮጵያ መድን እና አዳማ ከተማ ተጠባቂ መርሃ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድን እና አዳማ ከተማ ተጠባቂ መርሃ ግብር

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ መድን በ45 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ካሸነፈ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋል።
በአንጻሩ በ21 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው አዳማ ከተማ ማሸነፍ ከወራጅነት ቦታ ለመላቀቅ በሚያደርገው ትግል ትርጉም ያለው ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
የ25ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ያገናኛል።
ድሬዳዋ ከተማ በ26 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ29 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ማሸነፍ ለሁለቱም ቡድኖች ከወራጅ ስጋት ቀጠና ለመራቅ ያግዛቸዋል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተካሄዱ የ25ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከነማን፣ መቻል አርባምንጭ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።