የሎስ ብላንኮዎቹ እና መድፈኞቹ ፍጥጫ - ኢዜአ አማርኛ
የሎስ ብላንኮዎቹ እና መድፈኞቹ ፍጥጫ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ ከአርሰናል ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለም አግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ገዝቷል።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ከ80 ሺህ በላይ ተመልካች በላይ በሚያስተናግደው ሳንቲያጎ በርናባው ይደረጋል።
ባለፈው ሳምንት በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አርሰናል በኤምሬትስ ሪያል ማድሪድን 3 ለ 0 አሸንፏል።
የ15 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ በውድድሩ ለመቆየት በዛሬው ጨዋታ ውጤት የመቀልበስ ከባድ ፈተናን ማለፍ ይጠበቅበታል። ማድሪዳውያን ይሄን እናሳካዋለን እያሉ ነው።
ሪያል ማድሪድ “ፍጹም የማይቻለውን የማድረግ ተአምራዊ አቅም አለው” አልፎም “የተአምራቶች ቡድን ነው” የሚሉ ሙገሳዎችና አድናቆችን ቢያገኝም ከመድፈኞቹ በጣም የበረታ ፉክክር እንደሚገጥመው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።
አርሰናል በሪያል ማድሪድ እስከ አሁን በሻምፒዮንስ ሊግ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ተሸንፎ አያውቅም። በዚሁ ጥሩ ታሪኩ ለመቀጠል 90 ደቂቃዎች ይቀሩታል።
ሎስ ብላንኮሶቹ ወይስ መድፈኞቹ? የመጨረሻው ሳቅ የማነው? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የ35 ዓመቱ ፈረንሳዊ ፍራንስዋ ሌቲክሲየርን ተጠባቂውን ፍልሚያ በዋና ዳኝነት እንዲመሩ መድቧቸዋል።
በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት በሳን ሲሮ ስታዲየም ኢንተርሚላን ከባየር ሙኒክ ይጫወታሉ።
ኢንተርሚላን በመጀመሪያው ጨዋታ 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወቃል። ቡድኑ በአንጻራዊነት ከተጋጣሚው የተሻለ የማለፍ እድል አለው።
የ45 ዓመቱ ስሎቬኒያዊ ስላቫኮ ቪንቺች ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ባርሴሎና ቦሩሲያ ዶርትሙንድን፣ ፒኤስጂ አስቶንቪላን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።