ቀጥታ፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ልማትና የኢንቨስትመንት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቷል

ደብረ፤ ብርሃን ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ልማትና የኢንቨስትመንት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት ማሳየቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ ያሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።


 

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው፤ በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ልማትና የኢንቨስትመንት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት ማሳየቱን ተናግረዋል።

በቀጣይነትም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የዘርፉ ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት አስፈላጊው እገዛና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጡ ባለሃብቶች የቦታ አቅርቦት፣ የብድርና ሌሎችንም አገልግሎቶች በተሟላ መልኩ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፤ የከተማዋን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የሚያግዙ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በከተማው ያለውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እየተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል።


 

በዚህም በ2017ዓ.ም 24 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ምርት ለማሸጋገር ታቅዶ ባለፍት 9 ወራት ብቻ 20 እንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የሚደረገው ድጋፍና ማበረታቻም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በደብረ ብርሃን ከተማ ከ48 በላይ እንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም