ቀጥታ፡

የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታ ቁጥጥርና መከላከልን ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፦ የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታን የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የማጥፋት ሥራን ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ሩፋኤል(ዶ/ር) ገለፁ።

ኢንስቲትዩቱ የቆላ ዝንብና ገንዲ በሽታን ለመቆጣጠር ከናሽናል ኤርዌይስ ጋር በመተባበር በአውሮፕላን የሚደረግ ኬሚካል ርጭትን በተመለከተ የባለድርሻ አካላት ምክክር አካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ሩፋኤል(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ መንግስት የእንስሳት ልማት ዘርፍን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው።

ምርትና ምርታማነትን የሚጎዱ በሽታዎችን በምርምር እና በጥናት በመለየት የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የማጥፋት ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የእንስሳት ምርታማነትን ከሚጎዱ በሽታዎች መካከል የገንዲ በሽታ አንዱ መሆኑን አንስተው በሽታውን የምታስተላልፈውን የቆላ ዝንብ ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመሬት ለመሬት ኬሚካል ርጭት፣ እንስሳትን ጸረ ቆላ ዝንብ ኬሚካል በመቀባት እና በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት በማካሄድ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እየደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ባለፈው ሳምንት የቆላ ዝንብን መቆጣጠርና መከላከል የሚያስችል የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ከናሽናል ኤርዌይስ ጋር በመተባበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማዜ ብሔራዊ ፓርክ መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች ላይ የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አዲሱ እዮብ(ዶ/ር) በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የገንዲ በሽታ የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የናሽናል ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካፒቴን አበራ ለሚ በበኩላቸው ድርጅታቸው የግብርና ሚኒስቴር አውሮፕላኖችን በመጠቀም ለግብርና ስራ አጋዥ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም አውሮፕላኖቹን በመጠቀም የግሪሳ ወፍ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣ የቆላ ዝንብና ሌሎች አደጋዎችን ለመቆጣጠር የኬሚካል ርጭት እያካሄደ መሆኑን ገልጸው፥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም