ቀጥታ፡

በአቡዳቢ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ለህዳሴው ግድብ የ100 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ 

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ):-በአቡዳቢ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበር አባላት ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቂያ የድጋፍ ንቅናቄን በመቀላቀል የመቶ ሺ ዶላር ቦንድ ግዢ ፈጽመዋል።

በአቡዳቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዛሬ በተከናወነው የቦንድ ግዢ ስነ-ስርዓት የኮሚኒቲው የቦርድ አመራሮች በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ዑመር ሁሴን(ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገዋል።

የኮሚኒቲው ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብዱልናስር ሀሮ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ግድቡ በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የተባበረ ክንድ ዕውን እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

አምባሳደር ዑመር ሁሴን(ዶ/ር) በበኩላቸው የግድቡን ግንባታ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው ግድቡ መላው ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን በማሳረፍ ደማቅ የጋራ ታሪክ የተጻፈበት ዳግማዊ አድዋ ነው ብለዋል።

ግድቡ ይፋ ከሆነበት ዕለት አንስቶ የአቡዳቢ ኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበረሰቡን በማስተባበር ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የግድቡ ማጠናቀቂያ ንቅናቄን በመቀላቀል ላደረገው አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደሩ  በመላው የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ማድረጋቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም