ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኘ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ዘጠኝ ወራት 300 ሺህ ቶን የሚጠጋ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
በ2017 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ እንደ ሀገር ከቡና ንግድ የሚገኘውን ገቢ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 299 ሺህ 607 ቶን ቡና 1 ነጥብ 508 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 202 ሺህ ቶን የሚጠጋ ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ሲሰራ የቆየ ሲሆን አፈፃፀሙ 148 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አንስተዋል።
በዘንድሮው አመት ዘጠኝ ወራት የተገኘው ገቢ ከ2016 በጀት ዓመት 12 ወራት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር አፈፃፀሙ ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት ከአመት አመት በመጠንም በጥራትም እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ በዘንድሮው በጀት ዓመት 400ሺህ ቶን የቡና ምርት ወደተለያዩ አገራት በመላክ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዘርፉ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ዋና ዳይሬከተሩ፣ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በመጠንም ሆነ በገቢ የተሻለ ነው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ከቡና ንግድ የሚገኘውን ገቢ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እንደ ሀገር የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባሉት ሶስት ወራት 120 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንደሚቻል አፈጻጸሙ እንደሚያሳይ ነው የተናገሩት።
ለተገኘው ስኬት የቡና ኤክስፖርት ስርአቱ ላይ ሪፎርም መደረጉና ያረጁ ቡናዎች በአዲስ እንዲተኩ መደረጉ ተጠቃሽ እንደሆነም አብራርተዋል።
የቡና ምርቱ 84 ለሚደርሱ አገራት የተላከ ሲሆን ሳውዲአረቢያ፣ ጀርመን ፣አሜሪካ ፣ቤልጂየም እና ቻይና ከመዳረሻ አገራት መካከል ቀዳሚዎቹ መሆናቸው ተገልጿል።