ኢትዮጵያ እና ቬትናም በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቬትናም በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቬትናም በንግድ፣ በትምህርት እና ሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ዛሬ ተፈራርመዋል።
የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግሥታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋዊ የአቀባበል ስነ-ስርዓት አድርገዋል።
ከአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ሁለቱ መሪዎችና የልዑካን ቡድኖቻቸው የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በሁለቱ ሀገራት የተካሄዱ ማሻሻያዎችን እንዲሁም ለትብበር የሚሆኑ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተለይም የልምድ ልውውጥንና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
መሪዎቹ የትብብር ሰነዶች የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይም የተገኙ ሲሆን፥ በንግድ እና በትምህርት ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባና በሃኖይ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ የሚያመቻች የሲቪል አቪዬሽን ስምምነት ተደርጓል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬትናም ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሰረተ ከ50 አመታት በኋላ የመንግስት መሪ ያደረጉት የመጀመሪያ ይፋዊ የኦፊሴላዊ ጉብኝት መሆኑን የየጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።