ቀጥታ፡

ከተረጂነት በመላቀቅ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመሩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፦ የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም መተግበር የጀመሩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችና የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና የዘርፎች ዕቅድ አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የፌዴራል ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የለውጡ መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ሀገራዊ ሪፎርሞች አከናውኗል፡፡


 

መንግሥት የወሰዳቸው ሀገራዊ ሪፎርሞች እና የፖሊሲ ለውጦች ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት የተቋማትን የመፈጸም አቅም አሳድጓል ብለዋል፡፡

መንግሥት ህዝብ ውስጥ ሆኖ የሚሰራ እና ህዝብን የሚያዳምጥ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰብዓዊ ልዕልና እና ሀገራዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ያስፈልጋል የሚል ጽኑ መርህ እንዳላት በማንሳት፥ ይህም በሁሉም አፍሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ሚናዋም በምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር ሆናለች ብለዋል፡፡


 

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተደማጭነት ያጎለበቱና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።

በቀጣይም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እና ምርታማነትን ማሳደግና የተፅዕኖ አድማስን የማስፋት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ተረጂነትን በማስወገድ በሁሉም መስክ ራሷን እንድትችል እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም መቋቋም የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው ብለዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የበጋ መስኖና ሌሎችም ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችና የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ማማ እየወጣች ነው ብለዋል፡፡

በለውጡ መንግሥት የተከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ሪፎርሞች የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያለመልሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለላቀ ስኬት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡


 

በመድረኩ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው፥ በጀት ዓመቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ ትልልቅ ሀገራዊ የፖሊሲ ለውጦች የተደረጉበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን በማድረግ በመደበኛ እና ትይዩ ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት የነበረው የፋይናንስ ስርዓት የሀገር ውስጥ ምርትን ለውጭ ገበያ አቅርቦ ምንዛሪ ማግኘትን የሚያበረታታ እንዳልነበርም አውስተዋል።

የለውጡ መንግስት ይህን አሰራር በፖሊሲ ደረጃ በመቀየር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ ትክክለኛ የእድገት መንገድ እየተከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፖሊሲ ለውጡ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማጎልበት፣ የባንኮችን የቁጠባ አቅም በማሻሻል፣ የዲጂታል ግብይትን በማሳለጥ፣ የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት ማመጣቱንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም