የዞን አምስትና የምስራቅ አፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ውድድር በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የዞን አምስትና የምስራቅ አፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ውድድር በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፦የዞን አምስት እና የምስራቅ አፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ሚያዝያ 14 እስከ 16 ቀን 2017 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
በአፍሪካ ፕሬዝዳንታዊ ውድድር ላይ ከተለያዩ 44 የአለም ሀገራት የተውጣጡ ከ 300 በላይ ልዑካን ቡድን እንደሚሳተፉ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
ፌዴሬሽኑ የምስራቅ አፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ውድድር እና የአፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ዩኒየን ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት አስፋው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ውድድሩን ለማዘጋጀት ለአንድ አመት ያህል አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
በዞን 5 የምስራቅ አፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ኢትዮጵያ ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋን፣ ኬኒያ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ ፣ ኡጋንዳና ጅቡቲ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትሳተፍ መሆኑን ገልፀው በዚህም 26 ተወዳዳሪዎች ተመርጠው በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም 50 በግል የሚወዳደሩ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።
ውድድሩ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንደሚጀመር አስታውቀው ውድድሩን የሚመሩት አለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን ዳኞች ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ፕሬዝዳንታዊ ውድድር ሚያዝያ 15 ቀን 2017 የሚካሄድ ሲሆን አምስት ኢትዮጵያውያንና 32 አለም አቀፍ ዳኞች ውድድሩን እንደሚመሩት አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ዩኒየን ጠቅላላ ጉባኤ ሚያዚያ 16 ቀን 2017 እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
አህጉር አቀፍ ውድድሩ የወርልድ ቴኳንዶን ለማስተዋወቅ፣ተወዳዳሪዎች አህጉር አቀፍ ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ እና የሀገርን መልካም ገፅታ ለመገንባት አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ከስፖርታዊ ውድድሩ ባሻገር ሀገራችን ያለችበትን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እንዳለው ነው ያስታወቁት።
ውድድሩ እኤአ በ2028 ለሚደረገው የአለም ወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ስፖርተኞችን ብቁ ለማድረግ ከፍተኛ ልምድ የሚወሰድበት እንደሆነም በመግለጫቸው አንስተዋል።