ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ግጭቶችን ለመከላከልና ሀገራዊ የሰላም ግንባታን ለማሳደግ በትብብር መሥራት በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊነት ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ(ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትሩ ግጭትን መሠረት አድርጎ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ ተቋማትና የተለያዩ ዘርፎች ተቀናጅተው መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በሚያጠናክር እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን በሚያፀና መልኩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው በመመለስ እና የተረጋጋ ሕይወትን እንዲቀጥሉ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ሥራ አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መከላከልና ሲፈጠሩም በሰላማዊ ውይይት መፍታት ሰፊ ጥረት የሚጠይቅና ልዩ ልዩ ባህሪያት ያሉት በመሆኑ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና አጋር አካላት ጋር በትብብር መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊነት ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አልካብሮቭ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ግጭትን ለመከላከልና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አድንቀው ግጭት የመከላከልና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚደግፉ ቃል መግባታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።