የጎዳና ላይ ሩጫው የሀገር ውስጥ የስፖርት አልባሳት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማስተዋወቅ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የጎዳና ላይ ሩጫው የሀገር ውስጥ የስፖርት አልባሳት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማስተዋወቅ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የሀገር ውስጥ የስፖርት አልባሳት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማስተዋወቅ እና ያላቸውን የማምረት አቅም ለማሳየት ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ሚያዚያ 19 በሁለቱም ጾታዎች በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አበባ ታመነ በወቅቱ እንደገለጹት ውድድሩ በርካታ ዓላማዎችን ሰንቆ ይካሄዳል፡፡
ውድድሩ ገቢ ምርትን በመተካት ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቷቸውን የስፖርት አልባሳት ለማስተዋወቅ እና የማምረት አቅማቸውን ማሳየትን አላማ አድርጎ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግር ለመፍታት እና ዘርፉን ለማሳደግ የተጀመረው የኢትዮጵያን ታምርት ንቅናቄን ማስተዋወቅ ሌላው የውድድሩ አላማ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 ለማስተዋወቅ ውድድሩ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተር አስፋው ዳኜ በበኩላቸው በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከ34 ክለቦች የተውጣጡ 565 አትሌቶች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡
ውድድሩ ወደ ውጭ ሄደው መወዳደር ላልቻሉ አትሌቶች እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
በውድድሩ ከክልል፣ ከከተማ አስተዳደር እና የተለያዩ ክለቦች ተወዳዳሪዎችና ታዋቂ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ13ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች 1ኛ ለሚወጡ 300ሺህ ፣2ኛ ለሚወጡ 200ሺህ እንዲሁም 3ኛ ለሚወጡ ደግሞ የ100ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡