ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በንጹሕ መጠጥ ውሃ እና ኃይል አቅርቦት ላይ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በንጹሕ መጠጥ ውሃ እና ኃይል አቅርቦት ላይ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በንጹሕ መጠጥ ውሃ እና ኃይል አቅርቦት ዙሪያ በተከናወኑ ተግባራት እና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ በገጠርና በከተሞች የተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች የተገኘባቸው ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 76 ሚሊዮን ከፍ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

በተለይም ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የተከናወኑ ተግባራት የሚቆጠሩ ውጤቶች እንደተገኘ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲሁም በውጤት መጠናቀቃቸው ለተገኘው ስኬት መሰረት መጣሉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘም ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ ቦታዎች ላይ ከጸሃይ ኃይል በማመንጨት በርካታ አካባቢዎች መብራት እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቁመዋል።

ኃይል ቆጣቢ ማብሰያዎችን ተደራሽ የማድረግ ሥራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት 22 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ግድቤን በደጄ በሚል መሪ ሀሳብ ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ ውሃን የማሰባሰብ አሰራር ተዘርግቶ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

በዚህም በ200 ትምህርት ቤቶች ውሃን በማሰባሰብ ከተማሪዎች አልፎም ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የከርሰ እና የገጸ ምድር ውሃ በተመለከተ ያሉበትን ደረጃ ማወቅ እቅዶች ለማውጣት ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት መረጃ የማሰባሰብ ሂደቱ በተጠናከረ መንገድ ሲሰራበት መቆየቱንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም