ቀጥታ፡

በቅድመ አንደኛ ትምህርት በአካልና በአዕምሮ ብቁ ዜጋን በማፍራት አርአያ የሆነው ትምህርት ቤት

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፦ ደጀዝማች ወንድይራድ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት በአካልና በአዕምሮም ብቁ ዜጋን ለማፍራት አርአያ የሚሆን ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል።

ቅድመ መደበኛ ሕጻናት ተማሪዎች በተሻለ የማስተማር ሥነ-ዘዴ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ የወደፊት ስብዕናቸውን በላቀ ደረጃ መገንባት እንደሚያስችል የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

እውቁ የሥነ-ልቦና ምሁር ሲግመንድ ፍሮይድ እንደሚለውም በልጆች የመጀመሪያዎቹ 5 እና 6 ዓመታት ላይ የሚሰራው ሥራ የልጆችን ቀጣይ የህይወት አቅጣጫ የመወሰን አቅም አለው።

ልጆችን ቀለል ባለ መንገድ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ የትምህርት አቀባበል አቅማቸውን በማሳደግ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በዚህ ረገድ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የሚገኘው ደጀዝማች ወንድይራድ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት በቅድመ መደበኛ ትምህርት አሰጣጥ ላይ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በትምህርት ቤቱ የትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን ቃኝቷል።

በዚህም ትምህርት ቤቱ ምቹ መማሪያ አካባቢን ለህጻናት በመፍጠር፣ የህጻናት መማሪያና መጫወቻ ግብዓትን በማሟላት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ተመልክተናል።


 

መምህርት ኤደን ጌታሁን "ትምህርት በጫወታ" የተሰኘ የማስተማር ዘዴን በመከተል ህጻናት አካባቢያቸውን፣ ቀለማትን፣ እንስሳትን፣ ፊደላትን እንዲያውቁ በጫወታ በመታገዝ እያስተማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

መምህርት ትዝታ ምትኩ በበኩላቸው የምንከተለው የማስተማር ዘዴ ተማሪዎች በቀላሉ ትምህርት እንዲቀበሉ የሚያደርግ ውጤታማ ዘዴ ነው ብለዋል።


 

በትምህርት ቤቱ የቅድመ መደበኛ፣ መጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሰለሞን ክቤ፤ በትምህርት ቤቱ 1ሺህ 734 ህጻናት በቅደመ መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቅድመ መደበኛ ትምህርት ደረጃን ለማሳደግ ትምህርት ቤቱ በቂ የህጻናት መጫወቻ፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያ፣ ማረፊያና ምገባ አገልግሎት እንዲኖረው መደረጉን አብራርተዋል።

ህጻናቱ ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ መደበኛ ትምህርት ሲሸጋገሩ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

በደጀዝማች ወንድይራድ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ያለው ተሞክሮ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ኃይሌ ናቸው።

የትምህርት ግብዓትን በማሟላት ለትምህርት ጥራት መሻሻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡


 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው ህጻናት በአካልም በአዕምሮም ብቁ ሆነው ለትምህርት እንዲዘጋጁ ለማስቻል የቀዳማዊ ልጅነት ክብካቤ መርኃ ግብር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ለተማሪ ውጤት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ እንደ ደጃዝማች ወንድይራድ ቅድመ መደበኛ ምሳሌ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እንዲስፋፉ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ተግባር ተኮር ትምህርትን የዕለት ተዕለት ልምዳቸው እንዲያደርጉ ትምህርት ቢሮው እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ 229 የመንግስት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡

ደጃዝማች ወንድይራድ መጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1973 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ የተመሰረተው በ2000 ዓ.ም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም