ስፖርት ለሰላም ግንባታ ያለውን አበርክቶ ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው -ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሐመድ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 7/2017 (ኢዜአ)፦ስፖርት ለሰላም ግንባታ ያለውን አበርክቶ ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሐመድ ገለጹ።

"ስፖርት ለልማትና ለሠላም" በሚል መሪ ሐሳብ በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል።


 

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሐመድ በዚሁ ወቅት፤ በደምቢዶሎ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ ስፖርት ለልማትና ለሰላም ያለውን አበርክቶ ያሣየ ነው ብለዋል።

ስፖርት ንቁና ጤንነቱ የተሟላ ዜጋን ከማፍራት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፥ መንግስት ለስፖርት ልማት ዕድገት ትልቅ ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል።

በዚህም ስፖርትን ባህል ያደረገ ዜጋን ለማፍራት የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለ5ኛ ጊዜ የሚከበረውን ስፖርት ለልማትና ለሰላም ቀን በደምቢዶሎ ከተማ መከበሩ ዞኑ ባለፉት ጊዜያት ከነበረበት የሰላም እጦት በሕዝብ እና በመንግስት የጋራ ጥረት መውጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አሁን የተሟላ ሰላም የተገኘበት አካባቢ በመሆኑ ሰላሙን ለማጽናት ስፖርት ትልቅ ሚና እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ምክትል ቢሮ ሃላፊ ደሣለኝ ጥላሁን በበኩላችው፤ በክልሉ ስፖርትን ባህል ያደረገ ዜጋን ከመፍጠር አኳያ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ "አንድ ሄክታር የስፖርት ማዘውተሪያ ለአንድ ቀበሌ" ተብሎ ወደ ስራ የተገባው ኢኒሼቲቭ የማዘውተሪያ ቦታዎችን ችግር እየፈታ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገመቹ ጉርሜሣ በበኩላቸው፥ በዞኑ የተካሄደው የማህበረሰብ የስፖርት እንቅስቃሴ አከባቢው ሰላማዊ ለመሆኑ ማሣያ መሆኑን ገልጸው፤ስፖርት ለሠላም፣ ለልማት እና አንድነት ያለው ዋጋ በተግባር መታየቱን ጠቁመዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማሰራት የሚታወቀው ኢንስትራክተር ነጻነት ካሣ እንዳለውም፥ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አብሮነትና አንድነትን ማምጣት እንደሚችል በተግባር የታየበት ነው ብሏል።

ከማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ ተሣታፊዎች መካከል ኢብሳ ደበላ እና ደበላ ተርፋ እንዳሉትም፤ በከተማዋ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ሌሎች መርሐ ግብሮች መካሄዳቸው ከተማዋ ሰላማዊ ሁኔታ ላይ ለመሆኗ ማሣያ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የተካሄደው ስፖርታዊ እንቅስቃሴም ስፖርት ለልማት፣ ለአንድነትና አብሮነት ያለው ከፍተኛ ሚና የታየበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም