ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ግኝትንና የባንኮችን የቁጠባ አቅም አሳድጓል -የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 7/2017 (ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ግኝትንና የባንኮችን የቁጠባ አቅም አሳድጓል ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ በፋይናንስ ዘርፉ ስኬታማ ሀገራዊ የፖሊሲ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን በመከተል በመደበኛና በትይዩ ገበያ መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት ማጥበብ መቻሉን ተናግረዋል።

ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ እያስገቡ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ለተለያዩ ዘርፎች የውጭ ምንዛሬ በማቅረብ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን እያፋጠነ ነው ብለዋል።

ከማሻሻያው በፊት የነበረው የፋይናንስ ስርዓት የሀገር ውስጥ ምርትን ለውጭ ገበያ አቅርቦ ምንዛሪ ማግኘትን የማያበረታታ እንደነበርም ፕሬዚዳንቱ አውስተዋል።

አሁን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠረው ምቹ ዕድል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተገኘ ያለው ስኬት ማሻሻያው በጥራትና በውጤታማነት እየተመራ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፥ ይህም ትክክለኛ የእድገት መንገድ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፖሊሲ ለውጡ የባንኮችን የቁጠባ አቅም በማሻሻል፣ የዲጂታል ግብይትንና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱንም ጠቅሰዋል።

ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማምጣቱ የፖሊሲ ትግበራውን ትክክልኛነት ያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 125 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህም ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅትጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

በዲጂታል አመራጭ አማካኝነትም ባንኩ 9 ትሪሊዮን ብር ዝውውር መፈጸሙን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም