ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 5 ነጥብ 2 ቢለየን አረቦን ሰበሰበ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 7/2017 (ኢዜአ)፦በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን አረቦን መሰብሰቡን የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የዘጠኝ ወራት የስራ እንቅስቃሴን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ደሳለኝ አምባው ፈንዱ በባንክ እና በማይክሮፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ ላስቀመጡ ድርጅቶችና ግለሰቦች የመድን ሽፋን እንዲያገኙ በማስቻል የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲኖር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ የሚሰጣችውን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና በብቁ የሰው ሃይል እንዲመራ ሰፊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከአባል የፋይናንስ ተቋማት አረቦን የመሰብሰብ እና ኢንቨስት የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱንም ነው የገለፁት።

በባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት 5 ነጥብ 2 ቢሊየን አረቦን መሰብሰቡን አስታውቀው፤ ይህም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ11 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያለው መሆኑን ገልፀዋል። 

ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም ከተሰበሰበው  አረቦን ውስጥ 4 ነጥብ 73 ቢሊዮን ከመደበኛ ተቀማጭ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው 0 ነጥብ 47 ቢሊዮን ከወለድ አልባ ተቀማጭ ገንዘብ የተገኘ ነው ብለዋል።

ተቋሙ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት የገንዘብ አቅሙን ለማጠናከር የኢንቨስትመንት ላይ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የፈንዱን የኢንቨስትመንት ክምችት ወደ 12 ነጥብ 1ቢሊዮን ማድረሱን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም