ፋኦ የኢትዮጵያን የስርዓተ-ምግብ ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ፋኦ የኢትዮጵያን የስርዓተ-ምግብ ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 7/2017 (ኢዜአ)፦ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያን ምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ማዕቀፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፥ በዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የስርዓተ ምግብ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዴቪድ ላቦርድ (ዶ/ር) ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን ስርዓተ-ምግብ ለውጥ ላይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ስትራቴጂን ከፋኦ ዓለም አቀፍ ፍኖተ ጋር የማጣጣም ጉዳይ በውይይቱ ወቅት የተነሳ ሀሳብ ነው።
ስትራቴጂው ሁሉን አቀፍ እና መረጃን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ የምርት፣የማቀነባበር፣ ስርጭት እና ተጠቃሚነት ስርዓትን መፍጠር ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፥ ኢትዮጵያ የፋኦ ዓለም አቀፍ ፍኖተ ካርታ የሙከራ ፕሮግራም ከተመረጡ አምስት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያለውን ጠቀሜታ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በፕሮግራሙ እውቅና ማግኘቷ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ እና ግብርና ስርዓት ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላት ገልጸዋል።
በፍኖተ ካርታው አማካኝነት ኢትዮጵያ የቴክኒክ ድጋፍ፣ዓለም አቀፍ ልምድ እና ከአጋሮች ጋር ያላትን ትብብር እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የስርዓተ ምግብ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዴቪድ ላቦርድ (ዶ/ር) ፋኦ የኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ውስጥ የገጠሟትን ፈተናዎች ለመፍታት የወሰደቻቸውን እርምጃዎች ያደነቁ ሲሆን ይህም ለሌሎች በቀጣናው ለሚገኙ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ እና የፋኦ ትብብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና የፈጠራ ኢኒሼቲቮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።