በባለሙያ የማይፈፀም የእንሰሳት እርድ በቆዳ ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ከዘርፋ የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በባለሙያ የማይፈፀም የእንሰሳት እርድ በቆዳ ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ከዘርፋ የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፦በባለሙያ የማይፈፀም የእንሰሳት እርድ በቆዳ ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በእንሰሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ከጸጋው በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አለመሆኗን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የእንሰሳት ሀብት አጠቃቀም ከዘልማዳዊ አሰራር ባለመላቀቁ በተለይም የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪው ጥራት ያለው ጥሬ ዕቃ እንዳያገኝ ተግዳሮት ሆኗል።
እሴት የተጨመረባቸው የቆዳ ውጤቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ዕድላቸው ሰፊ ቢሆንም የእሴት ሰንሰለት ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን ነው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ የሚያሳየው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የእንስሳት እርባታው ሥጋን እንጂ ቆዳን ታሳቢ አለማድረጉን አንስተዋል።
ይህ አመለካከት ለእርድ የሚሰጠውን ትኩረት በመቀነስ የእንሰሳት ቆዳ ጥራት እንዲጓደልና ለሚፈለገው ጥቅም እንዳይውል ማድረጉን አመልክተዋል።
በዓላትን ተከትሎ በባለሙያ የማይፈፀም የእንሰሳት እርድ ደግሞ በቆዳ ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ከዘርፉ የሚጠበቀው ገቢ እንዳይገኝ እያደረገ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፣ ኢትዮጵያ የእንሰሳት ቆዳን ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የቆዳ ልማት ስትራቴጂ አውጥታ መተግበር ጀምራለች።
በስትራቴጂው በቆዳ ጥራት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በጥናት መለየታቸውንና ለዚህ የሚሆን መፍትሄ መቀመጡን አንስተዋል።
ከእንሰሳት እርባታ ጀምሮ የቆዳ ጥራትን ለማስጠበቅና በየአካባቢው የሚፈፀም የእንሰሳት እርድን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
አቶ ወንዱ ለገሰ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንስቲትዮትን ከአስር ዓመት በላይ በዋና ዳይሬክተርነት የመሩና በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ የእንሰሳት ቆዳ ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመምጣቱ ዋነኛ ምክንያት ህገወጥ እርድ ነው።
እርዱ በጥንቃቄና በባለሙያ ባለመፈፀሙ ቆዳው ላይ ጉዳት በማድረስ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ ዕቃ እንዳያገኙ አድርጓል ነው ያሉት።
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃገማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የጥራት መንደር ገንብታለች።
ይህን ዕድል በመጠቀም ከጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅርቦት ጥራት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ለባለሙያዎች የሥራ ላይ ሥልጠናን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።