የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ አካዳሚክ እና ትምህርታዊ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀ የበይነ መረብ ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል።
ውይይቱ የሩሲያ የመሬት አጠቃቀም፣ አስተዳደር እና ፕላኒንግ ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና ከኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር መስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለውን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት በትምህርት ዘርፍም ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሩሲያ የመሬት አጠቃቀም፣ አስተዳደር እና ፕላኒንግ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አሌክሳንደር ሊኒኮቭ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሊኖሩ ስለሚችሉ የትብብር መስኮች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
ሁለቱም ወገኖች በተማሪዎች እና መምህራን አካዳሚክ እንቅስቃሴ፣ በሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ትብብር፣ በምርምር ፕሮጀክቶች እና ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ኢዜአ በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።