የመላ ደቡብ ወሎ ዞን ስፖርታዊ ጨዋታዎች ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የመላ ደቡብ ወሎ ዞን ስፖርታዊ ጨዋታዎች ተጠናቀቀ

ደሴ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፡- ዘጠነኛው የመላ ደቡብ ወሎ ዞን ስፖርታዊ ጨዋታዎች በተንታ ወረዳ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።
በደሴ ከተማ ላለፉት አስር ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው ዘጠነኛው የመላው ደቡብ ወሎ ዞን የስፖርት ጨዋታ ዛሬ ከሰዓት ተጠናቋል።
በዚህም ተንታ ወረዳ በስፖርታዊ ውድድር 11 ወርቅ፣ 11 ብርና 10 ነሐስ በማምጣት አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሆኗል።
በስምንት ወርቅ፣ በአንድ ብር እና በአንድ ነሐስ አልቡኮ ወረዳ ሁለተኛ ሲሆን ኩታበር ወረዳ ደግሞ በሰባት ወርቅ፣ በአራት ብር እና በሁለት ነሐስ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል ሞላ እንደገለፁት ውድድሩ የተቀዛቀዘውን ስፖርት በማነቃቃት የዘርፉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አስተዋጽኦ አለው።
ሁሉንም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች በማሳተፍ በተካሄደው የመላ ደቡብ ወሎ ዞን ጨዋታዎች በ13 የስፖርት ዓይነቶች ከ2 ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች መሳተፋቸውን አውስተዋል።
በውደድሩ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ከ300 በላይ ስፖርተኞች ዞኑን ወክለው በመላው አማራ ክልል ጨዋታዎች ላይ እንዲሳተፉ መመረጣቸውንም አስረድተዋል።
በስፖርት የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር ተተኪ ስፖርተኛ ለመፍጠርም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችም እየተመቻቹ ነው ብለዋል።
የተንታ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ኃላፊና የልዑኩ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን መላኩ በበኩላቸው በውድድሩ የተሻለ ውጤት በማስመዝገባቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ውድድሩ አንድነታችንን ከማጠናከር ባለፈ ባህልን ለማስተዋወቅ አስችሎናል ብለዋል።
በማጠቃለያ ፕሮግራሙ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳን ጨምሮ የክልሉ፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አመራሮች፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ ስፖርተኞችና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።