ስፖርት ለአብሮነት፣ ለልማትና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ሚና የማጎልበት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሃመድ - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት ለአብሮነት፣ ለልማትና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ሚና የማጎልበት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሃመድ

አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ):-ስፖርት ለአብሮነት፣ ለልማትና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለውን ሚና የማጎልበት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሃመድ ገለጹ።
5ኛው ሀገር አቀፍ ስፖርት ለልማትና ለሰላም ቀን በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።
በውይይቱ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሃመድ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሣያስ ጅራ፣ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጥላሁን፣ የቄለም ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ ጉርሜሣን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።
በውይይቱ ስፖርት ለጤንነት፣ ለልማት፣ ለሰላምና ለአንድነት ያለውን ሚና ለማጠናከር እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሃመድ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ስፖርት ለሀገር ብልጽግና መረጋገጥ ሁለንተናዊ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።
ስፖርት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ፣ ለልማት እና ለአብሮነት እሴት መጎልበት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የወንድማማችነት ትርክትን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።
ስፖርት ጤናው የተጠበቀ ዜጋን በመፍጠር የበኩልም ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቄለም ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገመቹ ጉርሜሣ በዚሁ ወቅት፤ በዞኑ ለስፖርት እና የባህል እሴቶች መጎልበት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በዞኑ ስፖርት ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው እንዲሁም ለሰላምና ልማት አበርክቶውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲጎለብትም በሁሉም ወረዳዎች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ደሣለኝ ጥላሁን በበኩላቸው በክልሉ ለስፖርት በተሰጠው ትኩረት በአንድ ቀበሌ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ መደረጉን አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ12 ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ የሚከበረውን ስፖርት ለልማትና ለሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ በነገው ዕለት በደምቢዶሎ ከተማ የማህበረሰብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚካሄደም ተጠቁሟል።