ቀጥታ፡

በኮምቦልቻ የሃይል ተሸካሚ መስመር ላይ ባጋጠመ ብልሽት የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስተካከል ርብርብ እየተደረገ ነው

ደሴ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፡- በኮምቦልቻ የኤሌክትሪክ  ሃይል ተሸካሚ መስመር ላይ ባጋጠመ ብልሽት የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስተካከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የሰሜን ምስራቅ ሪጅን አንድ ዳይሬክተር አቶ በድሩ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኮምቦልቻ አንድ እና ኮምቦልቻ ሁለት 132 ኬሎ ቮልት ሀይል ተሸካሚ መስመር ላይ  ብልሽት አጋጥሟል።

ብልሽቱ ያጋጠመው ሁለት የሀይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች/ታወሮች/ ስርቆት ተፈጽሞባቸው መውደቃቸውን ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች፣ በደቡብ ወሎ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞን የተወሰኑ ወረዳዎችና ከተሞች ከትላንት ረፋድ ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጧል ብለዋል።


 

ችግሩን ለማስተካከል ጊዜያዊ የእንጨት ምሰሶ በመትከል ሀይሉን ለማስተካከልና አገልግሎቱን ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

አገልግሎቱ እስኪጀምር ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ህብረተሰቡ በሃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ስርቆት የፈጸሙትን ለህግ አካል ከመጠቆም ባለፈ የአካባቢውን መሰረተ ልማት ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም