ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የዲፕሎማሲ ዘርፉን አፈጻጸም አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ መድረክ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጓንም አንስተዋል።

እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተናገድ መቻሏንና የህብረቱ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧን ገልጸዋል።

ከአጎራባች ሀገራት ጋር ከወደብ እና የባህር በር ጉዳይ ጋር በተገናኘ የነበሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት መቻሉን ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃም የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎች የኢትዮጵያን አቅም እና ተጽእኖ ፈጣሪነት ይበልጥ እያጎለበቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም በኃይል መሰረተ ልማት ቀጣናውን ለማስተሳሰር ሰፋፊ ስራዎች ማከናወኗንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይታጠር ለቀጣናው አቅም እንደሆነ በተጨባጭ የታየበት መሆኑን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም