የ25ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብሮች

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

16 ጊዜ የሊጉ ዋንጫ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ31 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ32 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከቀኑ 9 ሰዓት ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሲዳማ ቡና በ29 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ሲይዝ ባህር ዳር ከተማ በ37 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የዕለቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻን ያገናኛል።

ሃዋሳ ከተማ በ21 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ወላይታ ድቻ በ37 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ ባለው ባህር ዳር ከተማ በግብ ክፍያ ተበልጦ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

መርሃ ግብሮቹ በዋንጫ ፉክክሩ እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሚባሉ ጨዋታዎች ናቸው።

በተያያዘ ዜና በተደረጉ የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች መቀሌ 70 እንደርታ ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና  ስሑል ሽሬ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም