የኢትዮ-አልጄሪያ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-አልጄሪያ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና አልጄሪያ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለፁ።
በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮ-አልጄሪያ 5ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሀገራቱን የዲፕሎማሲ ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ መስኮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ተጠናቋል።
ከሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን፤ የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት በማጠናከር በትብብር መስራት በሚያስችሉ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ በመምከር መስማማታቸው ተገልጿል።
በዚህም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና አካዳሚ፣ በኃይልና ማዕድን፣ በጋራ የቢዝነስ ምክር ቤት፣ በግብርና፣ በፈጠራ፣ በስፔስ ሳይንስ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በጤና እና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ፣ በባህልና ስፖርት መስኮች የኢትዮ-አልጄሪያን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚሁ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያና አልጄሪያ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።
የኢትዮ-አልጄሪያ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብርም ከሀገራቱ ታሪካዊ የወዳጅነት ትስስር የሚቀዳ ተምሳሌታዊ ግንኙነት መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ ጋር ያላትን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ በበኩላቸው እንደገለጹት ሀገራቱ በፓን አፍሪካኒዝም መርህ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማስቀጠል በትብብር ጠንከረው ይሰራሉ።
ኢትዮጵና አልጄሪያ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የአፍሪካን የፖለቲካ አንድነትና የኢኮኖሚ ውህደት ለማሳለጥ በከፍተኛ ኃላፊነት አንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የትብብር ስምምነቶቹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ከአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ ጋር ተፈራርመዋል።