ቀጥታ፡

ሆሳዕና አብሮነትንና ትህትናን የምንማርበት ሃይማኖታዊ በዓል ነው - ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ ሆሳዕና አብሮነትንና ትህትናን የምንማርበት ትልቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለፁ።

የዐቢይ ፆም የመጨረሻ ሳምንት የሆነው የሆሳዕና በዓል በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶችና ምእመናን በተገኙበት ተከብሯል።


 

በዚህ ወቅት ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሆሳዕና አብሮነትንና ትህትናን የምንማርበት ትልቅ ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን በአንድነት፣ በጋራ እና በመተሳሰብ ልናከብር ይገባልም ብለዋል።


 

የቅድስት ስላሴ ካቴድራል አገልጋይ ቀሲስ አብርሃም ተገኝ የሆሳዕና በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ትህትናን ለሰው ልጆች ያስተማረበት እለት መሆኑን ተናግረዋል።

የበዓሉ እሴት ፍቅርን በማብዛት፣ ወንድማማችነትን በማጎልበትና እርስ በእርስ በመተጋገዝ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የራስን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባል ብለዋል።


 

ምእመናን በዓሉን እርስ በእርስ በመዋደድና በመተሳሰብ እንዲሁም አንድነትን በማጠናከር ልናከብረው እይገባል ሲሉ የገለጹት ደግሞ ሌላው የቤተክርስቲያኑ አገልጋይ መልአከ ገነት ይትባረክ በርሄ ናቸው።                                                                                             

የሃይማኖት አባቶቹ ምዕመናን በእለት ተእለት ህይወታቸው ሰላምና አብሮነትን ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉም መክረዋል።

 መረዳዳትና አብሮነትን በማጠናከር ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጎን መቆም እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም