ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩ የትብብር መስኮች የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ላይ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ እና የአልጄሪያ አምስተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በስብሰባው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ እንዲሁም የሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

ከሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፤ የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት በማጠናከር በትብብር መስራት በሚያስችሉ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ በመምከር ከስምምነት እንደተደረሰ ተገልጿል።


 

በዚህም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና አካዳሚ፣ በኃይልና ማዕድን፣ በጋራ የቢዝነስ ምክር ቤት፣ በግብርና፣ በፈጠራ፣ ስፔስ ሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በጤና እና ፋርማሲዩቲካል ኢንዳስትሪ፣ በባህልና ስፖርት መስኮች የኢትዮ-አልጄሪያን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የትብብር ስምምነቶቹንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ከአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ ጋር ተፈራርመዋል።


 

በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የአልጄሪያ አምስተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም