ኢትዮጵያ በጃፓን እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ኦሳካ ኤክስፖ-2025 ላይ እየተሳተፈች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጃፓን እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ኦሳካ ኤክስፖ-2025 ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በኦሳካ የባሕር ወሽመጥ በምትገኘው ዩሜሺማ ደሴት በተጀመረው ኦሳካ ኤክስፖ-2025 እየተሳተፈች ትገኛለች።
ከዚህ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተካሄደው የኤክስፖው ይፋዊ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይም በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ከኦሳካ ኤክስፖ አሶሴሽን የውጭ ግንኙነት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ኪኩዎ ታኬ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን አስጀምረዋል።
አምባሳደሩ በዚህ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ጃፓን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና በጋራ ትብብር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የጃፓን መንግስት የአገራችንን የኤክስፖ ተሳትፎ እንዲሳካ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በኤክስፖው ቆይታ አገራችንን የሚገልጹ ፕሮግራሞች፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም አቅሞች በሰፊው እንደሚተዋወቁ አምባሳደር ዳባ ገልፀው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን እንዲጎበኙም ጋብዘዋል።
የኦሳካ ኤክስፖ አሶሴሽን የውጭ ግንኙነት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ኪኩዎ ታኬ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክና ባህሎች ባለቤት መሆኗን ገልጸው የአገራችን የኤክስፖው ተሳትፎ ስኬታማ እንዲሆንም ተመኝተዋል።
በስነ ስርዓቱ የአገራችን የቢዝነስ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም አቅሞችን ለታዳሚዎች ማስገንዘብ እንደተቻለ ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኤክስፖው “Designing Future Society for Our Lives” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ለቀጣይ ስድስት ወራት የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል።
160 የሚሆኑ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሳተፉ እና 28 ሚሊዮን በሚሆኑ ጎብኚዎች እንደሚጎበኝ ይጠበቃልም ተብሏል።