ቀጥታ፡

ሆሳዕና ትህትና እና ፍቅርን የምንማርበት ታላቅ በዓል ነው - ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ ሱራፌል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ ሆሳዕና ትህትና እና ፍቅርን የምንማርበት ታላቅ በዓል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌል ተናገሩ።

የ2017 ዓ.ም የሆሳዕና በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌል የሆሳዕና በዓል ምስጋናን የምንማርበት ነው ብለዋል።

ራስን ዝቅ ማድረግ የትህትና ምልክት መሆኑን ገልጸው፤ እለቱ ይህንን የምናስብበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን አክብሮት፣ ትህትና፣ ፍቅርና ራስን ዝቅ ማድረግ ታላቅነት መሆኑን በተግባር ያሳየበት ዕለት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

እንዲሁም እርስ በእርስ መረዳዳትን፣ አብሮነትን፣ መደጋገፍንና መተባበርን የሚያስተምር በዓል መሆኑን አክለዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ላጡ በመስጠትና የተቸገሩትን በማሰብ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ፍቅር በመግለጽ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከእምነቱ ተከታዮች መካከል አማኑኤል በላይ በዓሉን የተቸገሩትን በመደገፍና ላጡት በማካፈል ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ እንደሚያሳልፍ ተናግሯል።


 

በቤተክስቲያኒቱ ሲሚናሪስት ስለሺ ፍቅሩ በበኩሉ የሆሳዕና በዓል ራስን ዝቅ ማድረግ እና ትህትናን የተማርንበት ነው ብሏል።

በዓሉን የታመሙትን በመጠየቅና የተቸገሩትን በመርዳት እንደሚያሳልፉ የገለጹት ደግሞ ወጣት ጽዮን ዮሴፍ እና ወጣት ይታገሱ ዮሴፍ ናቸው።

በአሉን በደመቀ መንገድ በማክበራቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም