ቀጥታ፡

የኢትዮ-አልጄሪያ አምስተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና የአልጄሪያ አምስተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በሀገራቱ የጋራ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ እንዲሁም የኢትዮጵያ እና አልጀሪያ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

ከሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን፤ የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት በማጠናከር በትብብር መስራት በሚያስችሉ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ በመምከር ከስምምነት እንደተደረሰ ተገልጿል።

በዚህም በግብርና፣ በጤና፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በባህልና ስፖርት፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስኮች የኢትዮ-አልጀሪያን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማጠናከር ለመስራት የመከሩባቸው ጉዳዮች ናቸው።

የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ በአምስተኛ የኢትዮ-አልጄሪያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ትናንት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሀደራ አበራ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም