ከሙስና የፀዳ እና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ በመገንባት ሂደት ሚናችንን እናጠናክራለን - የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ከሙስና የፀዳ እና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ በመገንባት ሂደት ሚናችንን እናጠናክራለን - የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ ከሙስና የፀዳ እና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ በመገንባት ሂደት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅኔና መጽሐፍት ትርጓሜ መምህር ሊቀ ጉባኤያት አባ ተክለኃይማኖት፣ የእስልምና ሃይማኖት መምህር ሼህ አብዱ ሠይድ መሀመድ እና በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስ የአዲስ አበባ ሲኖዶስ ምክትል ፕሬዝዳንት ቄስ ዘላለም ቸርነት(ዶ/ር) በትውልድ ግንባታና ሙስና መከላከል ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅኔና መጽሐፍት ትርጓሜ መምህር ሊቀ ጉባኤያት አባ ተክለኃይማኖት ትውልድን በሥነ-ምግባር ማነጽና ሙስናን የመከላከል አስተምህሮ የዕምነት ተቋማትና የኃይማኖት አባቶች የምንጊዜም ስራ ነው ብለዋል።
በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት እንዲሁም ስርቆትን ለመከላከል እየሰሩ እንደሚገኙ በመግለጽ።
የትምህርት ተቋማት በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ በመገንባት የሙስና መከላከል ስራን ውጤታማ ለማድረግ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የእስልምና ኃይማኖት መምህር ሼህ አብዱ ሠይድ መሀመድ በበኩላቸው የሰው ልጅ ኑሮውን በወዙና በራሱ ጥረት መምራት እንዳለበት የሁሉም ኃይማኖት አስተምህሮና ምክር መሆኑን ገልጸዋል።
በእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮ ነፍስ ሁሉ በሰራችው ስራ ትያዘለች ያሉት ሼህ አብዱ፤ በዚህም በትውልድ ግንባታና ሙስና መከላከል ላይ የእምነት ተቋማት አስተምህሮ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስ የአዲስ አበባ ሲኖዶስ ምክትል ፕሬዝዳንት ቄስ ዘላለም ቸርነት(ዶ/ር) የራስ ያልሆነን ንብረት ለራስ ጥቅም ማዋል፣ ስርቆትና ታማኝነትን ማጉደል የኢትዮጵያውያን ባህል አይደለም ብለዋል።
በዚህም ሁሉም ዜጋ አትስረቅ የሚለውን አምላካዊ ቃል በመከተል ለተሻለ ሀገር ግንባታ በትብብር መስራትና መለወጥ እንደሚኖርበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሙስና እና ያልተገባ የጥቅም ትስስር የልማትና የመልካም አስተዳደር አቅርቦቶችን በማቀጨጭ ዜጎችን ለከፋ ድህነት የሚያጋልጥ ኢ-ሞራላዊ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደንበኞቻቸውን በተገቢው መንገድ የሚያገለግሉበትን ቀጣይነት ያለው ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
የመንግስትና የግል ተቋማት የሚመሩበት የአሰራር ሥርዓት እንዳላቸው ሁሉ የእምነት ተቋማትም የሚመሩበት የሕይወት ምንጭ የሆኑ ቅዱሳት መጽሐፍት መኖራቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም በየእምነት ተቋማት ኃይማኖታዊ አስተምህሯቸው በሙስና መከላከል ላይ ትምህርት በመስጠት በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።