በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል ውክልና አልሰጠሁም - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል ውክልና አልሰጠሁም - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል ውክልና አለመስጠቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል።
ካናዳን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ለሥራ ዜጎችን እንልካለን፡፡ ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ፍቃድ አግኝተናል በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ህገ-ወጥ ማስታወቂያዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እየዳረጉ በመሆኑ መሰል የማጭበርበር ተግባር እየፈፀሙ የሚገኙ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በውጭ ሀገር ስራ ስምሪቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወደ አውሮፓና አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል የሰጠው ውክልና የሌለ መሆኑን እየገለጽን ዜጎቻችን በስምሪቱ ተጠቃሚ ለመሆን ህጋዊ አማራጮችን ብቻ በመጠቀም ካላስፈላጊ ወጪ፣ እንግልትና ሌሎች አስከፊ አደጋዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
የሁለትዮሽ ስምምነት በተፈረመባቸው መዳረሻ ሀገራት የሥራ ዕድል ማግኘት ከፈለጉ የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ (lmis.gov.et) በመጠቀም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ በመመዝገብ ደህንነቱ የተረጋገጠ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ይሁኑ ሲልም መልዕክት አስተላልፏል፡፡