ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ለሚካሄደው ምክክር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 4/ 2017 (ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል ለሚካሄደው ምክክር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ሲቪክ ማህበራት አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ በዚህ ወቅት፥ በትግራይ ክልል ከግጭቶች ማግስት የተፈጠረውን ማህበራዊ ችግር ለመፍታት ብዙ መወያየትና መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


 

ኮሚሽኑ በክልሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንደሚገነዘብ ገልጸው፥ከዚህ ቀደም በክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ውይይቶች ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

መተማመንን ለመፍጠር ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ፤ እርስ በርስ ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ሲቪክ ማህበራት የማህበረሰቡን ድምፅ በምክክር መድረኮች ከማንፀባረቅ ባሻገር ሒደቱ አካታች እንዲሆን ለማድረግ የማይተካ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

“ኮሚሽኑ ገለልተኛ ነው ወይስ አይደለም” የሚለውን ቀርቦ በተግባር መፈተሸ እንደሚያስፈልግና በክልሉ የሚኖረው ሒደት የተለየ ስልት እንደሚያስፈልገው ከዛሬው ውይይት ተገንዝበናል ብለዋል።

ይህ ምክክር እንዲካሄድ ወይም እንዳይካሄድ ማድረግ የምንችለው እኛው ስለሆንን፤ ለሒደቱ በቁርጠኝነት መስራት ይገባናል ሲሉም አክለዋል።

ሰላም ብዙ አማራጮች ቢኖሩትም ዋነኛው የሰላም መንገድ ግን ምክክር መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከተሳታፊዎች በተነሱ ሀሳቦች ላይ አስተያየት የሰጡት ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ናቸው።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ክልልን ለማካተት ቁርጠኛነቱ እንዳለው ገልጸው፥ እኛና እናንተ ተባብለን ሳይሆን ስለእኛ ምክክር ብለን በሒደቱ ላይ የጋራ ኃላፊነት መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ለሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ሒደት አለመከተሉንና በትግራይ ክልልም የሕዝቡን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት አስቻይ ስልት እንደሚቀይስ አስታውቀዋል።

በቀጣይ በትግራይ ክልል ከማህበረሰቡ፣ ከመንግስት ኃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እንደሚደረጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ለሚያካሂደው ምክክር ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ መቅረቡን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም