ሠራዊቱ የሶማሊያን ሰላም በመጠበቅ ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው- ሜጀር ጀኔራል አዳምነህ መንግስቴ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ የሶማሊያን ሰላም በመጠበቅ ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው- ሜጀር ጀኔራል አዳምነህ መንግስቴ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሶማሊያን ሰላም በማስከበር ረገድ ውጤታማ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ በባይድዋ ሴክተር 3 የተገኙት የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል አዳምነህ መንግስቴ ገለጹ።
ሜጀር ጀኔራል አዳምነህ መንግስቴ፥ በሶማሊያ የተሰማራውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴን በባይደዋ በመገኘት ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት፥ በሁሉም መስክ ተልዕኳችሁን እየተወጣችሁ የምትገኙት የሴክተር 3 አመራርና አባላት በሀገር ወዳድነትና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የህዝብና የመንግስትን ተልዕኮ ሰንቃችሁ ደከመኝ ሰለቸኝ ባለማለት ስኬታማ ስራ በማከናወን ለትልቅ ድል መብቃትን በተግባር ማሳየት በመቻላችሁ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ የሶማሊያ የፀጥታ ኃይል ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ከአልሸባብ እንዲከላከሉ በማብቃትና ተልዕኮን በጋራ በመወጣት ውጤታማ ማከናወኑን አመልክተዋል።
የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊው አልሸባብ እኩይ ተግባሩን ማሳካት እንዳይችል አድርጋችሁ የህዝቡን ባህልና ወግ አክብራችሁ ተልዕኳችሁን መወጣት በመቻላችሁ ሃገራችንና ተቋማችን ኮርተውባችኋል ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የሴክተር 3 ዋና አዘዥ ብርጋዲየር ጀነራል በስፋት ፈንቴ በቀጣናው ስላለው ጠቅላላ ሁኔታ ስለ ሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም፤ ስለ አዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) እና ሌሎች ሥራዎች ገለጻ ማድረጋቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።