በአማራ ክልል የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬታማ ነበር- ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬታማ ነበር- ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም
ባህርዳር፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬታማ እንደነበር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም አስታወቁ።
በክልሉ ለምክክሩ የተሰበሰበው አጃንዳ ርክክብና የማጠቃለያ መርሐ ግብር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም እንደገለጹት፤ በክልሉ የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል።
በክልሉ የሕዝብ ወኪሎች የተሰበሰቡት አጀንዳዎችም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት የሚያግዙ አጀንዳዎች መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ይህም ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመነጋገርና በመወያየት እንዲሁም በመተማመን መስራት ባህል እንዲሆን ጭምር ያገዘ እንደሆነም ተናግረዋል።
የቀረቡ አጀንዳዎች ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ፣ሰላምና አብሮነት መጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ለዚህ ስኬታማነትም ሕዝቡ በሂደቱ በንቃት እንደተሳተፈው ሁሉ እስከ መጨረሻው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኮሚሽነሩ፥በአማራ ክልል የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የተካሄደው ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተቋማትና የሌሎችም ወኪሎች በተገኙበት ነው።