በልጆች ላይ ትኩረት ያደረገ ''ናኦታ'' የተሰኘ የአፋን ኦሮሞ መጽሔት ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በልጆች ላይ ትኩረት ያደረገ ''ናኦታ'' የተሰኘ የአፋን ኦሮሞ መጽሔት ተመረቀ
አዳማ ፤ሚያዚያ 4/2017( ኢዜአ)፡- በልጆች ላይ ትኩረት ያደረገና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚታተም ''ናኦታ'' የተሰኘ የአፋን ኦሮሞ መጽሔት ዛሬ ተመረቀ።
በአዳማ በተከናወነው የምረቃ መርሃ ግብር ላይ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምከትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንደሞ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ተስፋሁን ጎበዛይን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴልና የክልል የስራ ሀላፊዎችና የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙሃን የነገውን ትውልድ በተሻለ መልኩ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው።
በተለይ ህጻናት የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽ መሆናቸው የሀገሪቷን ተንሳዔ እውን ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ገንቢ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
'ናኦታ' መጽሔት ልጆች ስለሀገራቸው ወጥ የሆነ አረዳድ እንዲኖራቸውና አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።
ለመጽሔቱ ተደራሽነት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አበክሮ መስራት እንዳለበት ጠቁመው፤ ሕጻናት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን በማበረታታት ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው እንቅስቃሴ የመንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማት የቅርብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምከትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንደሞ በበኩላቸው በሕጻናትና በታዳጊዎች ላይ የሚጻፉ ጽሁፎች የጋራ ትርክት ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
መጽሔቷ በኢ-ልቦለዳዊና በልቦለዳዊ ይዘቶች እያዝናኑ የልጆችን ሥነምግባር ለማነጽ፣ ልጆች የንባብ ልምድን እንዲያዳብሩ ዓይነተኛ መሳሪያ ሆና ታገለግላለችም ብለዋል።
በለተይ ሕጻናትን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በቀላሉ በማስተዋወቅ ልጆች በእውቀትና ክህሎት እየበለጸጉ እንዲረዱ ለመጽሄቷ መጠናከር ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የንባብ ባሕልን ማሳደግ የሚገባው መጽሐፍትን የልጆች ጓደኛ ማድረግ ሲቻል በመሆኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳዘጋጀው 'ናኦታ' ልጆች ላይ ትኩረት ያደረገ መጽሔት ሲዘጋጅ ባለድርሻ አካላት ሊያግዙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ እንዳመለከቱት፤ ድርጅቱ በተለያዩ ቋንቋዎች ሕትመቶችን እያዘጋጀ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ አንጋፋ ተቋም ነው።
ዛሬ የተመረቀው የመፅሄት ዓምዶቹ ሲቀረጹና ስያሜ ሲሰጣቸው የልጆችን ሥነ ልቦና፣ ግብረገብነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ አብሮነትን፣ አሳታፊነትንና ሌሎች ጉዳዮችን እንዲያካትት ተደርጎ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጀመረውን የለውጥ ጉዞ በመቀጠል ለዓመታት ተዘንግተው የኖሩትን ህጻናትና ታዳጊ ልጆችን ታሳቢ ያደረገ የልጆች መጽሄት በአማርኛ ቋንቋ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ማሳተም መጀመሩን ገልፀዋል።
አሁን ደግሞ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ “ናኦታ” የተሰኘች የሕጻናትና የልጆች መጽሔትን አዘጋጅቶ ማሳተም መጀመሩን አስታውቀዋል።
በቀጣይም በሌሎች ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።