ኢንዱስትሪዎች ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪዎች ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ
አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ ሚና በማበርከት ላይ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከመጋቢት 29 ጀምሮ "ከሸማችነት ወደ አምራችነት" በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ - አዲስ አበባ ታምርት የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ-ርዕይ የማጠቃለያ መርሐ ግብር የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና አምራቾች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በአውደ-ርዕዩ ከ250 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች መሣተፋቸው ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት፥ በአውደርዕዩ የገበያ ትስስርና ምርትን የማስተዋወቅ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከ3 ሺህ 700 በላይ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ያነሱት ምክትል ከንቲባው፥ የማምረት አቅማቸው ከ64 በመቶ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርትና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎቹን የማምረት አቅም ለማሳደግና ለዘርፉ መነቃቃት የሚያግዝ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዘላቂ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መሠረት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ምርት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲመለሱም ማድረጉ ተገልጿል።
በዛሬው መርሐ ግብር የደረጃ ሽግግር ያደረጉ አምራቾች እውቅና እንደሚሰጣቸው ተጠቁሟል።