የአምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው- ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው- ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ "ከሸማችነት ወደ አምራችነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከመጋቢት 29 ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።
ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በዘርፉ ያሉ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ፎረም እየተደረገ ይገኛል።
በፎረሙ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፤ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣የባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተሳትፈውበታል።
ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)፥ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በመፍታት ውጤታማነታቸው እንዲሻሻል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያሻ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ማነቆ የሆኑ የማምረቻ ቦታ ችግሮችን ለመፍታት የክላስተር አሰራር እንዲተገበር ጥሪ አቅርበዋል።
ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ባንኮች ብድር በመስጠት እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተቀናጀ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ መናገራቸውንም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ ዛሬ ይጠናቀቃል።