ለታላቅ ሃገር በፅናት ዘብ የቆምን ጠንካራ ሠራዊት ነን - ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቅ ሃገር በፅናት ዘብ የቆምን ጠንካራ ሠራዊት ነን - ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦ለታላቅ ሃገር በፅናት ዘብ የቆምን ጠንካራ ሠራዊት ነን ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ገለጹ።
ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በሠራዊቱ የግዳጅ ቀጠና ተገኝተው ተልዕኮ በመፈፀም ላይ የሚገኙ የሠራዊት አባላትንና በስልጠና ላይ የሚገኙ የመቶና የጓድ አመራሮችን ስልጠና በመመልከት ሰራዊቱን አበረታተዋል።
ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ፥ ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምታደርገውን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ መግታት የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ የሠራዊታችን የዝግጁነት ደረጃ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ታላቅ ዝና ፣ታሪክና ክብር ያላት ሀገር ናት ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ፥ ክብሯንና ዝናዋን እንደጠበቀች ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ደግም የዚህ ትውልድ በተለይም ደግሞ የሠራዊቱ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ፣ የህዝቡን ሠላም ለማደፍረስና ፈጣን የልማት ዕድገቷን ለመጎተት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልዕኮ የተቀበሉ ተላላኪ ባንዳዎች ሴራ ማክሸፉን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ክብር እንደማንደራደር ጠላቶቻችን ጠንቅቀው ያውቁታል ነው ያሉት።
ዕዙ በማንኛውም ጊዜ፤በየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘር ጥቃትን መከላከል በሚያስችለው የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ሌተናል ጄኔራሉ ለሰራዊቱ አባላት አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ዝግጁነታቸውን የበለጠ በማጠናከር ስራዎችን ማከናወንና ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።