ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጪው የትንሳኤ በዓል በቂ የምርት አቅርቦት ተዘጋጅቷል-የኢትዮጵያ ሕብረት ስራ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2017 (ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጪው የትንሳኤ በዓል በቂ የምርት አቅርቦት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ሕብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጫልቱ ታምሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ኮሚሽኑ የገበያ ሰንሰለቱን ወጥነት ያለው፣ ህጋዊና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ለማድረግ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
 
አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ የሚሸጥባቸው የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዬኖችን በስፋት ማቋቋም፣የገበያ ትስስር መፍጠርና ዘርፉን ከህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች እንዲጠበቅ ማድረግን ለአብነት አንስተዋል፡፡
 
በዚህም ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲያገኝ በማድረግ የኑሮ ውድነቱ የማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ለዘንድሮው የፋሲካ በዓል የምርት እጥረት እንዳይከሰት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህም የግብርና ምርቶች፣የኢንዱስትሪ፣ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
 
ይህም ግብይቱ የተረጋጋ እንዲሆን እና የምርት እጥረት እንዳይከሰት በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

ኢዜአ የሉሜ አዳማ የገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒዬን እና የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ሕብረት ስራ ዩኒዬን ለበዓሉ በቂ ምርት ለማቅረብ ያደረጉትን ዝግጅት አስመልክቶ ቅኝት አድርጓል፡፡
 
ዩኒዬኖቹ በሰብል ምርቶች ፣በቁም እንስሳት፣ በዶሮ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎችም ለበዓሉ በቂ ምርት ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
የሉሜ አዳማ የገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒዬን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳዬ ቸሩ በዚሁ ወቅት፤ለበዓሉ የጤፍ፣ የስንዴና ሌሎች ምርት እንዲሁም ዱቄት በስፋት ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
 
በተጨማሪም በቂ የቁም እንስሳትና የዶሮ አቅርቦት እንዲኖር እየሰራ ሲሆን አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ሕብረት ስራ ዩኒዬን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሮባ በበኩላቸው፥ ዩኒዬኑ ለመጪው የትንሳኤ በዓል ሽንኩርትን ጨምሮ በቂ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አቅርቦት እንዲኖር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
 
ለበዓሉ ሁሉንም የምርት ዓይነቶች በኤግዚቢሽንና ባዛሮች እንዲሁም በመሸጫ ሱቆች በማቅረብ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
ምርቶቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመላክ የገበያ ማረጋጋት ስራውን በስፋት ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም