በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጪው የትንሳኤ በዓል በቂ የምርት አቅርቦት ተዘጋጅቷል - የኢትዮጵያ ሕብረት ስራ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጪው የትንሳኤ በዓል በቂ የምርት አቅርቦት ተዘጋጅቷል - የኢትዮጵያ ሕብረት ስራ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጪው የትንሳኤ በዓል በቂ የምርት አቅርቦት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ሕብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጫልቱ ታምሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የገበያ ሰንሰለቱ ወጥነት ያለው፣ ህጋዊና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ለማድረግ ኮሚሽኑ የተለያዩ የአሰራር ስርአቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ የሚያስረክብበት የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዬኖችን በስፋት ማቋቋም፣ የገበያ ትስስር መፍጠርና ዘርፉን ከህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች እንዲጠበቅ ማድረግን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በዚህም ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲያገኙ በማድረግ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ማድረግ ማቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ለዘንድሮው የፋሲካ በዓል የምርት እጥረት እንዳይከሰት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የግብርና ምርቶች፣ የኢንዱስተሪ፣ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ግብይቱ የተረጋጋ እንዲሆንና የምርት እጥረት እንዳይከሰት በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
ኢዜአ የሉሜ አዳማ የገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒዬን እና የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ሕብረት ስራ ዩኒዬን ለበዓሉ ያደረጉትን ዝግጅት አስመልክቶ ቅኝት አድርጓል፡፡
ዩኒዬኖቹ በሰብል ምርቶች፣ በቁም እንስሳት፣ በዶሮ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎችም ለበዓሉ በቂ ምርት ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሉሜ አዳማ የገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒዬን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳዬ ቸሩ በዚሁ ወቅት፤ ለበዓሉ እሴት የተጨመረባቸውን የሰብል ምርቶችን ማለትም ጤፍ፣ ስንዴ ባቄለና ሌሎችንም ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የቁም እንስሳትና በዶሮ በቂ አቅርቦት እንዲኖር እና አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ሕብረት ስራ ዩኒዬን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሮባ በበኩላቸው ዩኒዬኑ ለፋሲካ በዓሉ በቂ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አቅርቦት እንዲኖር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ለፋሲካ በዓል ሁሉንም የምርት ዓይነቶች በኤግዚቢሽንና ባዛሮች እንዲሁም በመሸጫ ሱቆች በማቅረብ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምርቶቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ወደ ሌሎች አካባቢዎችም በመላክ የገበያ ማረጋጋት ስራውን በስፋት ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡