የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመከላከያ ልዕልናና የላቀ ብቃት ማሳያ ነው- አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመከላከያ ልዕልናና የላቀ ብቃት ማሳያ ነው- አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 3/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመከላከያ ልዕልና እና የላቀ ብቃት ማሳያ እንዲሁም የሪፎርሙ ስኬት ማረጋገጫ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትር አይሻ ዛሬ የኢፌዴሪ አየር ኃይልን የጎበኙ ሲሆን ተቋሙ ያስመዘገባቸውን ስኬቶችም አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ብቃቱን ለማላቅ ያከናወናቸውን ተግባራት ለማስቀጠልና ለማፅናትም ሚኒስቴሩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
አየር ኃይሉ ብቃቱን ለማሳደግና ለማላቅ በቴክኖሎጂ ዕድገትና በማያወላውል ቁርጠኝነት ሀገራዊ ግዴታውን በመወጣት ረገድ እያሳየ ያለው ብቃት በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡
አየር ኃይሉ በተለይም የጥገና ወጪን በማዳንና በራስ አቅም ለመስራት የሄደባቸው ርቀቶች የሀገርን ሃብት በከፍተኛ መጠን በማዳን ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኘ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
ሚኒስትሯ የተቋሙን መሰረተ ልማቶች በማዘመንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችም በስኬት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ነው ያነሱት።
የተቋሙን ዝግጁነትና ስትራቴጂካዊ ዕድገት የበለጠ ለማረጋገጥና ለማፅናትም ሚኒስቴሩ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ቃል ገብተዋል።
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው አየር ኃይሉ በሰው ኃይል፣ በጥገናና በመሰረተ ልማት ግንባዎች ዘርፍ የደረሰበትን ደረጃ በማስመልከት ገለጻ አድርገዋል።
ዋና አዛዡ የሚኒስቴሩን ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮችን በማቅረብ ውይይት መካሄዱን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።