አስተዳደሩ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ - ኢዜአ አማርኛ
አስተዳደሩ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።
የ2017 የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ ከመጋቢት 29 ጀምሮ "ከሸማችነት ወደ አምራችነት" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው፡፡
ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በዘርፉ ያሉ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች ላይ የሚዳስስ ባለድርሻ አካላት የተገኙበት ፓናል ውይይት ተካሂዷል።
አቶ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ በዘርፉ ያለውን መልካም አጋጣሚዎች ለማስፋት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም ቢሮው በመዲናዋ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የመስሪያ ቦታን ጨምሮ የፋይናንስ፣ የኃይል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና በገበያ ትስስር ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ፍቃዱ ደግፌ በለውጡ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለመደገፍ የፖሊስ ማሻሻዎችን ጨምሮ በርካታ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ እና የበጀት ፖሊሲ ሪፎርም መደረጉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ የብድርና የውጭ ምንዛሬ እጥረት መቅረፍ ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ምርት በማሳደግ ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አስፋው አበራ ባንኩ እንደ ፖሊሲ ባንክነቱ የአምራቾች ኢንዱስትሪ ችግር በጥናት በመለየት ለመፍታት እየሰራ ነው ብለዋል።
ከብድር አቅርቦት ጋር ያለውን የዋስትና ጉዳይ ለመፍታት የሊዝ ፋይናንስ ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ ማሽነሪዎችን እንደዋስትና በመያዝ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባንኩ ከብድር አቅርቦት ባሻገር የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት አምራች ኢንዱስትሪውን እየደገፈ ይገኛል ነው ያሉት።
የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ በበኩላቸው ኮሚሽኑ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማበረታት የፖሊሲ ማሻሻያን ጨምሮ የአግልግሎት አስጣጡን ሪፎርሞች መደረጉን ተናግረዋል።
የካፒታል እቃዎችን ያለ ቀረጥ ማስገባትን ጨምሮ የታሪፍ ማሻሻያዎች መደረጉን ገልጸዋል።
የስኬት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳምጠው አለማየሁ ባንኩ የአምራች ኢንዱስትሪው እንዲያድግ በልዩ ትኩረት ብድር እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
የአዲስ ካፒታል ፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሳይ ሂንሴኔ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ለመደገፍ የማምረቻ መሣሪያዎችን ገዝቶ በማቅረብ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ነው ያሉት።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮችን በማቃለል የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ሊደገፉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ማነቆ የሆኑ የማምረቻ ቦታ ችግሮችን ለመፍታት የክላስተር አሰራር ሊተገበር እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለማቃለል ባንኮች ብድር በመስጠት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ሊደገፉ እንደሚገባ ጠቁመው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም ነው የገለጹት።