ቀጥታ፡

በየአካባቢው ያሉ ቅርሶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም የማሳደግ ስራ ይጠናከራል

ሮቤ፤ ሚያዝያ 3/2017 (ኢዜአ)፡- በየአካባቢው ያሉ አገራዊ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ከማስመዘገብ ባሻገር ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ የማስተዋወቅና የማልማት ስራ እንደሚጠናከር የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ገለጸ። 

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ ቅርሶችን ዘላቂነት ማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ የሚዲያ ጉብኝት እየተካሄደ ነው።  


 

የሚዲያ አባላት ጉብኝቱ በተለይም በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች በዩኔስኮ በቋሚ ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶችን ማዕከል በማድረግ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረቢራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለሥልጣኑ አገራዊ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ከማስመዘገብ ባሻገር በማስተዋወቅና ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ነው። 

ባለሥልጣኑ ባለፉት ዓመታት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት 12 ቅርሶችን በሚዳሰሱና ስድስት ቅርሶችን ደግሞ በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ በዩኔስኮ በቋሚነት እንዲመዘገቡ ማድረጉን አመልክተዋል። 

''ቅርሶችን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ብቻውን ግብ አይደለም'' ያሉት ኃላፊው ቅርሶቹ ይበልጥ እንዲተዋወቁና እንዲለሙ በማድረግ ለአገር ኢኮኖሚ እንዲውሉ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች በሚገኙ መዳረሻዎች እየተደረገ የሚገኘው የሚዲያ ቡድን ጉብኝትም ይህንኑ ዓላማ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን አስረድተዋል። 

የሚዲያ ቡድኑ ባለፉት ቀናት የመልካ ቁንጡሬ የአርኪዮሎጂ ስፍራ፣ የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ፣ የጌዴኦ መልክዓ ምድርና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል። 

ቡድኑ ጉብኝቱን በመቀጠል በዛሬው ዕለት በምሥራቅ ባሌ ዞን የሚገኙ የድሬ ሼህ ሁሴን ጥንታዊ መስጂድና በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች መዳረሻዎችን እንደሚጎበኝ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። 

በአገሪቱ የሚገኙ መዳረሻዎች እንዲለሙና ይበልጥ እንዲተዋወቁ ማድረግ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ፍሰት በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማሳደግ ያግዛል ያሉት ደግሞ በቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ናቸው። 


 

የሚዲያ አባላት ጉብኝቱ በተለይ በቅርቡ በዩኔስኮ በቋሚ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ይበልጥ እንዲተዋወቅና ተደራሽ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ እንዳለው አስረድተዋል። 

የባሌ ዞን ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ህንዲያ ሁሴን በበኩላቸው ጉብኝቱ በዞኑ የሚገኙ በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦች እንዲተዋወቁና ያለባቸው ተግዳሮቶች እንዲለዩ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ተናግረዋል።  


 

በጉብኝቱ በአገር ውስጥ የሚገኙ የመንግሥትና የግል የመገናኛ ብዙኃን አባላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም