ቀጥታ፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት በትምህርት ፍትሐዊነት፣ ምዘና እና ፈተና አስተዳደር ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል - አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሰባት አመታት በትምህርት ፍትሐዊነት፣ ምዘና እና ፈተና አስተዳደር ላይ ለውጥ ማምጣት መቻሉን የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ።

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለይ በፈተና አስተዳደር ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

ለውጡ ኩረጃን ከማስቀረት ባሻገር ፈተናን ባልተገባ መንገድ ሲጠቀሙበት የቆዩ አካላትን መቆጣጠር አስችሏል ነው ያሉት።

ከለውጡ በፊት የነበረው የፈተና አሰጣጥ የፈተና አስተዳደሩ ላይ ጫና ከመፍጠሩም ባለፈ በሀገር ተረካቢ ዜጎች ላይ የስነ-ልቦና ጫና ሲፈጥር መቆየቱን ነው የጠቆሙት።

በተለይ ከ2014 እስከ 2016 ዓ/ም ኩረጃን ከመቆጣጠር አኳያ ለውጥ መታየቱን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የፈተና አሰጣጥና የምዝገባ ሂደቱ በቴክኖሎጂ መደገፉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ለሕትመት፣ ለተማሪዎችና ለመምሕራን የሚከፈሉ የተለያዩ ወጪዎችን መቀነስ መቻሉን ነው ያነሱት።

በተጨማሪም የፈተና ውጤትን በወቅቱ ለመግለጽና ቅሬታዎች በፍጥነት የሚቀርቡበትን አካሔድ ተግባራዊ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።

ለውጡ በትምህርት ምዘና ላይ በተመረጡ የክፍል ደረጃዎች ተማሪዎች በስርአተ ትምህርቱ የተቀመጡትን አጥጋቢ የመማር ብቃቶችን እንዲይዙ አድርጓል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ፕሬዝዳንት ዩሐንስ በንቲ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከለውጡ አመታት በኋላ በፈተና አሰጣጡ ላይ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም ከፈተና አስተዳደርና ምዘና አኳያ የተከናወኑ ማሻሻያዎች ተማሪዎች ቀደም ብለው ለፈተና በአግባቡ እንዲዘጋጁ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ ዓመታት በፊት በተለይም ኩረጃ እንደ ባሕል የሚታይበት ወቅት እንደነበር አስታውሰው የተከናወኑ ማሻሻያዎች በእውቀቱ የሚተማመን ትውልድ ለማፍራት የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ፈተና እንደ አንድ ግብአት የሚታይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በለውጡ የተከናወኑ ተግባራት ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ከ1938 ዓ/ም ጀምሮ የ34 ሚሊዮን ተፈታኝ ተማሪዎችን መረጃ አደራጅቶ ማስቀመጡ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም