ቀጥታ፡

ግዙፉ የቻይና ኩባንያ ለኢትዮጵያ የግብርና ማሽነሪዎችን የማቅረብ ፍላጎት አለው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 3/2017(ኢዜአ)፦የቻይና ብሔራዊ ማሽነሪ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ለኢትዮጵያ ገበያ የግብርና ማሽነሪዎችን የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በቻይና ብሔራዊ ማሽነሪ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሊ ዢያሁ ከተመራ ከፍተኛ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ውይይቱ በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ተካሄዷል።

ልዑኩ በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ ትልቅ አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን የወከሉ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ኩባንያዎቹ ባላቸው ግዙፍ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የማምረት አቅም በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ተሳትፎ የግብርና ዘርፉን በማዘመን ረገድ የሚኖረው ሚና ላይ ምክክር ተደርጓል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ ከተለመደው አሰራር በመውጣት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን አርሶ አደሮችን በማደራጀት ኩታገጠም (ክላስተር) እርሻን በስፋት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና ለዚህም ሰፊ የግብርና ማሽነሪዎች ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል።

ኩባንያዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ የግብርና ማሽነሪዎችን በማቅረብ ይህንን ፍላጎት እንዲያሟሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ በግብርና ምርት ኤክስፖርት፣ በአነስተኛ መስኖ ቴክኖሎጂ፣ በሀገር ውስጥ የግብርና ማሽነሪዎችን ማምረት እና በሌሎች የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የቻይና ባለሀብቶች እንዲሰማሩም ጠይቀዋል።

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የቻይና ብሔራዊ ማሽነሪ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሊ ዢያሁ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች ምርት፣ በግብርና ልማትና በግብርና ምርምር የካበተ ልምድ እንዳለው አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም